በ2ኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች እየተሰጠ የሚገኘው የስራና ተግባር ትምህርት በሚፈለገው ደረጃ ውጤታማ እንዲሆን ሁሉም ባለድርሻ ኃላፊነቱን መወጣት እንደሚገባው ተገለጸ።
(ጥቅምት 6/2019 ዓ.ም) የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ትምህርት ቢሮ የ2ኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ዋና ርዕሳነ መምህራንና የመማር ማስተማር ምክትል ርዕሳነ መምህራንን ጨምሮ የቴክኒክና ሙያ ማሰልጠኛ ኮሌጅ ዲኖችና የክፍለከተማ የሁለቱ ስርአተ ትምህርት ትግበራ ቡድን መሪዎች በተገኙበት ውይይት አካሂዷል።
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ትምህርት ቢሮ ኃላፊ ክቡር ዶክተር ዘላለም ሙላቱ በከተማ አስተዳደሩ አዲሱ ስርአተ ትምህርት ተግባራዊ መደረጉን ተከትሎ ከ2017 ዓ.ም ጀምሮ የስራና ተግባር ትምህርት በ2ኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ተግባራዊ መደረጉን አስታውሰው ትምህርቱ ተማሪዎች ከንድፈ ሀሳብ ትምህርት ባሻገር በሚመርጡት የሙያ መስክ ሰልጥነው ቀጣይ ህይወታቸውን ስኬታማ ማድረግ እንዲችሉ ታስቦ ተግባራዊ እንደመደረጉ ርዕሳነ መምህራን በአቅራቢያቸው ከሚገኙ የቴክኒክና ሙያ ማሰልጠኛ ኮሌጆች ጋር ትስስር በመፍጠር ተማሪዎችን ማብቃት እንደሚገባቸው አስገንዝበዋል።
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ትምህርት ቢሮ ምክትል ቢሮ ኃላፊ አቶ ተስፋዬ አበራ በበኩላቸው በከተማ አስተዳደሩ ዘንድሮ የተጨመሩ 11 የሙያ መስኮችን ጨምሮ በጠቅላላው 22 የሙያ መስኮች እየተሰጠ መሆኑን ገልጸው ተማሪዎቹ ሙያዊ ክህሎታቸውን አሳድገው ውጤታማ እንዲሆኑ ቢሮው ከቴክኒክና ሙያ ማሰልጠኛ ኮሌጆች ጋር ቅንጅት ፈጥሮ እንደሚሰራ አመላክተዋል።
የአዲስ አበባ ከተማ ቴክኒክና ሙያ ቢሮ ከትምህርት ቢሮ ጋር በጋራ በመሆን የሙያና ተግባር ትምህርት ተማሪዎች ውጤታማ እንዲሆኑ በትኩረት እንደሚሰራ የቢሮው ምክትል ኃላፊ አቶ አለማየሁ ሚጄና አስታውቀዋል።
በ2ኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች የሚሰጠው የሙያና ተግባር ትምህርት በሚፈለገው ደረጃ ውጤታማ እንዲሆን ቢሮው በሙያው የሰለጠኑ መምህራንን አወዳድሮ በመቅጠር ላይ መሆኑን የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ትምህርት ቢሮ ምክትል ቢሮ ኃላፊ አቶ አሊ ከማል በሰጡት ማብራሪያ ገልጸዋል።
በመርሀግብሩ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ትምህርት ቢሮ የስርአተ ትምህርት ማበልጸጊያና ትግበራ ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ ጌታቸው ታለማ እና የቴክኒክና ሙያ ቢሮ ዳይሬክተር አቶ ነጋ የመወያያ ሰነድ አቅርበው በተሳታፊዎች ውይይት ተካሂዷል።
.