(ነሀሴ 22/2018 ዓ.ም) የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ትምህርት ቢሮ የልዩ ፍላጎትና ጎልማሶች መሰረታዊ ትምህርት ዳይሬክቶሬት በ2ኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች በ2019 የትምህርት አመት የልዩፍላጎት ተማሪዎችን ፍላጎት በመለየት በትምህርታቸው ውጤታማ ማደርግ በሚቻልበት አሰራር ዙሪያ ላይ በትኩረት እየሰራ እንደሚገኝ ገልጻል፡፡
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ትምህርት ቢሮ የልዩ ፍላጎትና ጎልማሶች መሰረታዊ ትምህርት ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ ገመቺስ ፍቃዱ በከተማ አስተዳደሩ በሚገኙ 1ኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች የተለያዩ የድጋፍ መስጫ ማዕከላት ተቋቁመው ለልዩ ፍላጎት ተማሪዎች የተለያዩ ድጋፎችን በመስጠት ላይ መሆናቸውን አስታውሰው ተማሪዎቹ ወደ 2ኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ተዘዋውረው መማር በሚጀምሩበት ወቅት ድጋፍ ማድረግ ስለሚገባ ተቋማቱ ተማሪዎቹን ከቅበላ ጀምሮ ፍላጎታቸውን በአግባቡ ለይተው የትምህርት አገልግሎቱ ተጠቃሚ ማድረግ እንደሚገባቸው አስገንዝበዋል፡፡
ዳይሬክተሩ አያይዘውም የልዩ ፍላጎት ተማሪዎች ትምህርታቸውን በአግባቡ ተከታትለው ውጤታማ መሆን የሚችሉት ፍላጎታቸውን መሰረት ያደረገ ልየታ በማካሄድ የተለያዩ ድጋፎችን ማድረግ ሲቻል በመሆኑ ርዕሳነ መምህራንም ሆኑ የልዩ ፍላጎት ትምህርት መምህራን የተማሪዎቹን ፍላጎት መሰረት ያደረገ ድጋፍ ማድረግና ትምህርትቤቶችን ለልዩ ፍላጎት ተማሪዎች ምቹ እንዲሆኑ መስራት እንደሚገባቸው አስገንዝበዋል፡፡
.