የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የተማሪ ወላጅ ማህበር የመማር ማስተማር ስራው ውጤታማ እንዲሆን እያበረከተ የሚገኘው አስተዋጽኦ ከፍተኛ መሆኑ ተገለጸ።
(ሚያዚያ 15/2018 ዓ.ም) ማህበሩ የከተማና የክፍለ ከተማ ስራ አስፈጻሚዎች በተገኙበት የ2018 ዓ.ም ሶስተኛ ሩብ አመት እቅድ አፈጻጸሙን እና በትምህርት ተቋማት ያካሄደውን የክትትልና ድጋፍ ግብረ መልስ የገመገመበትን መርሀግብር አካሂዷል።
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደርና የኢትዮጵያ የተማሪ ወላጅ ማህበር ፕሬዘዳንት አቶ ሀሰን ሽፋ በመርሀግብሩ መክፈቻ ባስተላለፉት መልዕክት ማህበሩ በ2018 ዓ.ም 3ኛ ሩብ አመት ከአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ትምህርት ቢሮ ጋር በጋራ በመሆን የተማሪዎች ውጤትና ስነምግባር እንዲሻሻል ባከናወናቸው የተለያዩ ተግባራት ውጤታማ መሆኑን አስታውሰው በተለይም የተማሪ ወላጆች በዕውቀት ፣ በጉልበትና በገንዘብ አስተዋጽኦ እንዲያደርጉ ማህበሩ የተለያዩ የግንዛቤ ማስጨበጫ ስራዎችን ሲያከናውን መቆየቱን አመላክተዋል።
አቶ ሀሰን አያይዘውም ማህበሩ በቀጣይ በትምህርት ቤቶችና በወላጆች መካከል የቅርብ ግንኙነት በመፍጠር የተማሪዎች ውጤትና ስነምግባር እንዲሻሻል የሚያደርገውን ክትትል አጠናክሮ የሚቀጥል መሆኑን በመግለጽ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ትምህርት ቢሮ ማህበሩ ውጤታማ እንዲሆን እያደረገ ለሚገኘው ድጋፍ ምስጋና አቅርበዋል።

.