ቢሮው ስታንዳርዱን የጠበቀ የ6ኛ እና 8ኛ ክፍል ከተማ አቀፍ ፈተና በማዘጋጀት ተማሪዎችን ውጤታማ ለማድረግ በትኩረት በመስራት ላይ መሆኑ ተጠቆመ።
(መስከረም 19/2019 ዓ.ም) የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ትምህርት ቢሮ የ2018 የትምህርት ዘመን የ6ኛ እና 8ኛ ክፍል ከተማ አቀፍ ፈተናን ከየትምህርት አይነቱ ተመርጠው በመጡ መምህራን ማስገምገም ጀምራል።
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ትምህርት ቢሮ ምክትል ቢሮ ኃላፊና የዘርፉ አስተባባሪ አቶ ሳምሶን መለሰ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ትምህርት ቢሮ ስታንዳርዱን የጠበቀና የተማሪዎችን ብቃት በአግባቡ መለካት የሚችል ከተማ አቀፍ የ6ኛ እና 8ኛ ክፍል ፈተናዎች እንዲዘጋጅ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በቅንጅት ሲሰራ መቆየቱን አስታውቀዋል።
ምክትል ቢሮ ኃላፊው አያይዘውም በ2018 የትምህርት ዘመን በሁሉም የትምህርት አይነት የተዘጋጀው ከተማ አቀፍ ፈተና በመምህራን መገምገሙ በ2019 የትምህርት ዘመን የተማሪዎችን ብቃት የሚለካና ስታንዳርዱን የጠበቀ ፈተና ለማዘጋጀት የሚያስችል መሆኑን ጠቁመው ፈተናውን የሚገመግሙ መምህራን ፈተናው በተዘጋጀው ስፔክ መሰረት መዘጋጀቱን በመገምገም ትክክለኛ ግብረመልስ ማቅረብ እንደሚጠበቅባቸው አስገንዝበዋል።
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ትምህርት ቢሮ የፈተና ዝግጅትና አስተዳደር ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ በለጠ ንጉሴ በበኩላቸው በየአመቱ የሚዘጋጀው ከተማ አቀፍ የ6ኛ እና 8ኛ ክፍል ፈተና በሀገር አቀፍ ደረጃ የተቀመጠውን የፈተና ቢጋር መሰረት አድርጎ እንደሚዘጋጅ አስታውሰው የፈተና ግምገማው ከመምህራን ባሻገር በቀጣይ በየደረጃው በሚገኙ የስርአተ ትምህርት ባለሙያዎች እንደሚገመገም አመላክተዋል ።
.