የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ትምህርት ቢሮ የልዩ ፍላጎትና ጎልማሶች መሰረታዊ ትምህርት ዳይሬክቶሬት የልዩ ክፍል ተማሪዎችን (special class students) ለመመዘን እና ከክፍል ወደ ክፍል ለማዘዋወር የተዘጋጀ ረቂቅ መመሪያ ላይ ከባለድርሻ አካላት ጋር ውይይት አካሄደ፡፡
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ትምህርት ቢሮ የልዩ ፍላጎትና ጎልማሶች መሰረታዊ ትምህርት ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ ገመቺስ ፈቃዱ በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ትምህርት ቢሮ ስር 34117 ተማሪዎች በ12 አይነት ልየታ ተደርጎ በአካታች፤ በልዩ ክፍልና ልዩ ትምህርት ቤት ትምህርት እየተሰጠ መሆኑን ተናግረው ፤ በልዩ ክፍል የሚማሩ ተማሪዎችን መሰረት ያደረገ የምዘና እና የክፍል ወደ ክፍል ዝውውር መመሪያ ባለመኖሩ መመሪያውን ማዘጋጀት ማስፈለጉን ገልጸዋል፡፡
ዳይሬክተሩ መመሪያው በየደረጃው በሚገኙና ብቃታቸው በተረጋገጠ የልዩ ፍላጎት ትምህርት ባለሙያዎች እና መምህራን እንዲሁም በስርአተ ትምህርት ባለሙያዎች መዘጋጀቱንና በመምህራን ፤ ርእሰ መምህራን ፤ ተዘዋዋሪ መምህራንና ሌሎች የሚመለከታቸው የትምህርት አካላት አስተያየት በመቀበል ረቂቅ መመሪያው ብቁ ይዘት እንዲኖረው ለማድረግ ውይይት መደረጉን ገልፀዋል ::
ረቂቅ መመሪያው የቢሮው የስርዓተ ትምህርት ባለሙያ በሆኑት አቶ ሰለሞን ወንድሙ አማካኝነት ቀርቦ ከትምህርት ሚኒስቴር ፣ ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ፣ ከስራና ክህሎት ቢሮ ፣ ከአካል ጉዳተኞች ማህበር ፣ ከሊያ የፋውንዴሽን ፣ ከዲቦራ ፋውንዴሽን ፣ ከረቂቅ ትምህርት ስልጠና ማእከል ፣ ከተለያዩ ተቋማት የመጡ ባለሙያዎች በተገኙበት ውይይት ተደርጎበታል፡፡
.