አዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ትምህርት ቢሮ የሚዲያ ይዘት ማበልፀግና ስርጭት ዳይሬክቶሬት የትምህርት በሬዲዮ አጀማመርና አካሄድ ላይ በ11ዱ ክፍለ ከተሞች በተደረገ ድጋፍና ክትትል ግብረመልስ ላይ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር ውይይት አካሂዷል፡፡
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ትምህርት ቢሮ ምክትል ቢሮ ሃላፊ አቶ ዲናኦል ጫላ በውይይቱ ላይ ተገኝተው ባስተላለፉት መልእክት የድጋፍና ክትትሉ ውጤት ትምህርት በሬዲዮ በመንግስት ትምህርት ቤቶች በአግባቡ እየተሰራ እንደሆነ ያሳያል ሲሉ ጠቁመው ትምህርት በሬዲዮ ድጋፍ ሰጪ ብቻ ሳይሆን የመደበኛ ስርዐተ ትምህርት አንዱ አካል እንደሆነ በመውሰድ በግል ትምህርት ቤቶችም ትኩረት ተሰጥቶት ሊሰራበት እንደሚገባ ተናግረዋል፡፡
የውይይቱ ተሳታፊዎችም የትምህርት በሬዲዮ ማስተላለፊያ ጣቢያን በመጠቀም የሚተላለፉ ትምህርቶች ለተማሪዎች ማመር ማስተማር ስራችን አጋዥ እንደሆኑ በመገንዘብ ለተግባራዊነቱ የበኩላቸውን አስተዋጽኦ እንዲያደርጉ በማለት አሳስበዋል፡፡
የሚዲያ ይዘት ማበልፀግና ስርጭት ዳይሬክተር ወ/ሮ የውብዳር አያሌው ቢሮው በአዲሱ ስርዓተ ትምህርት የተማሪዎችን ውጤት ለማሻሻል ብሎም ትምህርትን በቴክኖሎጂ በማስተማር ሀገር አቀፍና አለማቀፍ ተወዳዳሪ እንዲሆኑ እየሰራ መሆኑን ተናግረው በእውቀት ላይ የተመሰረተ ድጋፍና ክትትል በማድረግ ትምህርትን በቴክኖሎጂ የመደገፍ ተግባራችንን አጠናክረን ለመቀጠል ግብአት የሚሆኑ ነጥቦች ከግብረመልሱ እናገኛለን ብለዋል አያይዘውም የትምህርት በሬዲዮ አተገባበር ላይ የስራ አቅጣጫ ሰጥተዋል፡፡
በውይይቱ የ2018 ዓ.ም 1ኛ ሩብ አመት ትምህርት በሬዲዮ አጀማመር ክትትልና ድጋፍ የተገኙ ዋና ዋና ግኝቶች እና ቀጣይ ሊተገበሩ የሚገባቸው ነጥቦች ላይ ትኩረት ያደረገ ሰነድ የትምህርት በሬዲዮ ስርጭት ጣቢያ ኃላፊ በሆኑት አቶ አብይ ተፈራ አማካኝነት ቀርቦ ውይይት ተደርጓል፡፡