የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ትምህርት ቢሮ የመምህራንና የትምህርት አመራር ልማት ዳይሬክቶሬት የቅድመ አንደኛ ደረጃ ትምህርት ውጤታማ ለማድረግ በተዘጋጁ ሞጁሎች ዙሪያ ለመምህራን፣ለአስተባባሪዎች እንዲሁም የክላስተር ማዕከላትን ጨምሮ በየደረጃው ለሚገኙ ሱፐርቫይዘሮች ሲሰጥ የቆየውን የአቅም ግንባታ ስልጠና አጠናቋል።
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ትምህርት ቢሮ የመምህራንና የትምህርት አመራር ልማት ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ ሀብታሙ ሀይሉ ስልጠናው በዋናነት በአራት ሞጁሎች የተካተቱ ይዘቶችን ምሰረት አድርጎ ሲሰጥ መቆየቱን ጠቁመው ሰልጣኞቹ በጫወታ የማስተማር ስነዘዴ አተገባበርን ፣ ለማስተማሪያ ኮርነሮች የሚያስፈልጉ መርጃ መሳሪያዎች አዘገጃጀትና አጠቃቀም እንዲሁም በእንግሊዘኛ ትምህርት ሲለበስ እና የክላስተር ሱፐርቫይዘሮችና አስተባባሪዎች መምህራን ውጤታማ እንዲሆኑ በምን መልኩ መደገፍ እንደሚገባቸው የአቅም ግንባታ ስልጠና መውሰዳቸውን አስታውቀዋል።
ዳይሬክተሩ አያይዘውም ሞጁሎች በኮተቤ ትምህርት ዩኒቨርሲቲ ምሁራን መዘጋጀታቸውን እና በቢሮ የሚገኙ አራት ዳይሬክቶሬቶች ማለትም የመምህራን ልማት፣የቀዳማይ ልጅነትና ዘርፈ ብዙ እንዲሁም ሁለቱ ስርአተ ትምህርቶችና የአጠቃላይ ትምህርት ሱፐርቪዥን ዳይሬክቶሬቶች መገምገማቸውን አስታውሰው ስልጠናው ከትምህርት ቀናት ውጭ ዘወትር ቅዳሜና እሁድ ለአምስት ቀናት በተግባር ተደግፎ ሲሰጥ መቆየቱን አመላክተዋል።መርሀግብሩ የአሰልጣኞች ስልጠና እንደመሆኑ የስልጠናው ተሳታፊዎች በየትምህርት ቤቱ ለሚገኙ መምህራን ተመሳሳይ የግንዛቤ ማስጨበጫ ስልጠና መስጠት የሚገባቸው መሆኑን አቶ ሀብታሙ አስገንዝበው የክላስተር ሱፐርቫይዘሮች በየማዕከላቸው ለሚገኙ የመንግስትና የግል የቅድመ አንደኛ ትምህርት ቤቶች ተመሳሳይ ስልጠና በመስጠት ሞጁሎቹ በአግባቡ ተግባራዊ እንዲሆኑ ኃላፊነታቸውን እንዲወጡ ጥሪ አቅርበዋል።በመርሀግብሩ ማጠቃለያ ስልጠናውን በአግባቡ ተከታትለው ላጠናቀቁ ሰልጣኞችና በአሰልጣኝነት ለተሳተፉ አካላት የዕውቅና ሰርተፊኬት መሰጠቱን ከስራ ክፍሉ ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።