በክፍለ ከተማው ከሚገኙ የትምህርት ተቋማት መካከል ቃሌ 1ኛ ደረጃ ትምህርት ቤት የመማሪያ ክፍሎችን ጨምሮ ለተለያዩ የአስተዳደር ስራዎች የሚያገለግሉ ክፍሎችን ያካተተ የG+4 መንትያ ህንጻ እና G+1 የመመገቢያ አዳራሽ እንዲሁም ቀጨኔ ደብረሰላም 2ኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ደረጃቸውን ጠብቀው የተገነቡ የ3በ1 ሁለገብ ሜዳና የእግር ኳስ መጫወቻ ሜዳ ተመርቆ ለአገልግሎት በቅቷል።
የጉለሌ ክፍለ ከተማ አስተዳደር ዋና ስራ አስፈጻሚ አቶ ወልዴ ወገሴ የክፍለ ከተማው አስተዳደር ትምህርት ቤቶች የነገ የሀገር ተረካቢ ዜጎች የሚፈሩባቸው ተቋማት መሆናቸውን በመገንዘ የተለያዩ ፕሮጀክቶችን በመገንባት ለአገልግሎት በማብቃት ላይ መሆኑን አስታውሰው በቃሌ አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት በ4 ወር ውስጥ ደረጃውን የጠበቀ የመማሪያ ክፍሎችን ያካተተ መንትያ ህንጻ እና የመመገቢያ አዳራሽ በማስገንባት ለአገልግሎት እንዲበቃ መደረጉን በመግለጽ በቀጨኔ ደብረሰላም 2ኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ደረጃውን ጠብቆ የተገነባው የስፖርት ማዘውተሪያ ሜዳ ሀገራችን በቀጣይ አመታት አሸናፊ ብሔራዊ ቡድን ለመገንባት ያስቀመጠችው ግብ ስኬታማ እንዲሆን የሚያስችል መሆኑን አመላክተዋል።
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ትምህርት ቢሮ የቢሮ ኃላፊ አማካሪ ወይዘሮ አበበች ነጋሽ በበኩላቸው የጉለሌ ክፍለ ከተማ አስተዳደር ለትምህርት ሴክተሩ ቅድሚያ በመስጠት በዚህ መልኩ ደረጃቸውን የጠበቁ የመማሪያ ክፍሎችን እና የመመገቢያ አዳራሽን የያዙ ህንጻዎችን ጨምሮ የስፖርት ሜዳዎችን በከፍተኛ በጀት አስገንብቶ ለአገልግሎት በማብቃቱ ምስጋና አቅርበው ግንባታዎቹ የተማሪዎች ውጤትና ስነምግባር እንዲሻሻል የሚያበረክቱት አስተዋጽኦ ከፍተኛ መሆኑን በመጠቆም ፕሮጀክቶቹ በከፍተኛ በጀት ተገንብተው ለአገልግሎት እንደመብቃታቸው የትምህርት ቤቶቹ ማህበረሰቦች በአግባቡ በመገልገል ለቀጣዩ ትውልድ እንዲያስተላልፉ ጥሪ አቅርበዋል።
በክፍለ ከተማው በሚገኙ ትምህርት ቤቶች የተገነቡ የመማሪያ ክፍሎችም ሆኑ የመመገቢያ አዳራሾችና የስፖርት ማዘውተሪያ ሜዳዎች ተማሪዎች ምቹ በሆነ ሁኔታ ስታንዳርዱን መሰረት ያደረገ ትምህርት ተምረውው ውጤታማ እንዲሆኑ የሚያስችል መሆኑን የጉለሌ ክፍለ ከተማ አስተዳደር ትምህርት ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ በርኬ ቤቲ ገልጸው ፕሮጀክቶቹ በዚህ መልኩ ደረጃቸውን ጠብቀው ተገንብተው ለአገልግሎት እንዲበቁ አስተዋጽኦ ላበረከቱ አካላት ምስጋና አቅርበዋል።