ከኬንያ Food For Education ከተባለ ተቋም የመጡ ልዑካን ቡድን አባላት በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ስር እየተከናወነ በሚገኘው የተማሪዎች ምገባ ስርዓት ላይ ልምድ ልውውጥ አካሂደዋል::
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ትምህርት ቢሮ ምክትል ቢሮ ኃላፊ አቶ ሳምሶን መለሰ በልምድ ልውውጡ ላይ በመገኘት የተማሪዎች ምገባ ከ2012 ዓ.ም ጀምሮ በከተማ አስተዳደሩ በሚገኙ ትምህርት ቤቶች 300 ሺ ተማሪዎች በመያዝ የተጀመረ መሆኑን ገልፀው አሁን ላይ 900 ሺ ለሚሆኑ ቅድመ 1ኛ ፣ 1ኛና መካከለኛ ደረጃ ተማሪዎች በቀን ሁለት ጊዜ ምገባ እንደሚደረግ ገልፀዋል::
ቶ ሳምሶን ተማሪዎች የተመጣጠኑ ምግቦች መመገብ በመጀመራቸው በትምህርት አቀባበልና ውጤት ላይ ከፍተኛ ልዩነት መመዝገቡን ተናግረው ለዚህም በ6ኛ እና 8ኛ ክፍል የታየው የተማሪ ውጤት መሻሻል ማሳያ ይሆናል ብለዋል:: አያይዘውም መንግስት ከፍተኛ በጀት በመመደብ ውጤታማ የትምህርት ስርዓት ለመዘርጋት እየሰራ ያለው ስራ በዓለም አቀፍ እና አፍሪካ ደረጃ እውቅና ያገኘንበት እና ለሌሎች ልምድ መስጠት የቻልንበት ነው ብለዋል::
የ Food for Education ዋና ዳይሬክተር ሻሎም ኒድኩ በበኩላቸው የልምድ ልውውጥ ልዑካን ቡድኑ አባላት መንግስት የትምህርት ውጤት መሻሻል ላይ ትልቅ ስራ እየሰራ መሆኑን ያዩበት እና የትምህርት ቤት መሰረተ ልማትን ጨምሮ በተማሪ ምገባ ስርዓት ያየነው ተጨባጭ ስራ ለሀገራችን ትልቅ ልምድ የምንወስድበት ነው ብለዋል::
የልምድ ልውውጡ አባላት በደጃዝማች ወንድይራድ ቅድመ አንደኛ አንደኛና መካከለኛ ደረጃ ትምህርት ቤት በመገኘት የምገባ ሥርዓቱንና በትምህርት ቤቱ ያለውን የከተማ ግብርና ስራዎች ተመልክተዋል::
በጉብኝቱ የኬንያ Food For Education ተቋም ዋና ዳይሬክተር ሻሎም ኒድኩን ጨምሮ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ትምህርት ቢሮ ምክትል ቢሮ ኃላፊ አቶ ሳምሶን መለሰ ፣ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ትምህርት ቢሮ ምክትል ቢሮ ኃላፊ አቶ ወንድሙ ዑመር ፣ የምገባ ኤጀንሲ ዋና ዳይሬክተር ወ/ሮ ፀዳለች ሚካኤል እና የሚመለከታቸው አካላት ተገኝተዋል::