Announcement በተፋጠነ ትምህርት ፕሮግራም አሰጣጥ ሂደት ላይ ምልከታ ተደረገ::

በተፋጠነ ትምህርት ፕሮግራም አሰጣጥ ሂደት ላይ ምልከታ ተደረገ::

07th March, 2026

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ትምህርት ቢሮ በተለያዩ ምክንያቶች የትምህርት እድል ላላገኙ ፣ ትምህርታቸውን ላቋረጡ  ወይም  በእድሜያቸው መማር ከሚገባቸው  ክፍል ወደ ኃላ ለቀሩ ተማሪዎች እየሰጠ  ባለው በተፋጠነ ትምህርት ፕሮግራም  አሰጣጥ ሂደት ላይ ምልከታ ተደርጓል::

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ትምህርት ቢሮ ምክትል ቢሮ ኃላፊ አቶ አሊ ከማል እና የልዩ ፍላጎት አካቶ ትምህርትና ጎልማሶች መሰረታዊ ትምህርት ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ ገመቺስ ፈቃዱ በለሚ ኩራ ክፍለ ከተማ መሪ 1ኛ እና መካከለኛ ደረጃ ትምህርት ቤት እና ጉለሌ ክፍለ ከተማ በሚገኘው ቁስቋም 1ኛ ደረጃ ትምህርት ቤት በመገኘት የተፋጠነ ትምህርት አሰጣጥ ሂደት ላይ ምልከታ አካሂደዋል::

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ትምህርት ቢሮ ምክትል ቢሮ ኃላፊ አቶ አሊ ከማል በትምህርት ቤቶቹ ምልከታ ባደረጉበት ወቅት በ44 ትምህርት ቤቶች እድሜያቸው ከ9-12 የሚሆን ከ2600 በላይ ተማሪዎች  የተፋጠነ ትምህርት እየወሰዱ እንደሆነ ገልፀው ትምህርት ቤቶቹም ተገቢውን እውቀት ለተማሪዎች ለማስጨበጥ እየሰሩ መሆኑን ተናግረዋል::

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ትምህርት ቢሮ የልዩ ፍላጎት አካቶ ትምህርትና ጎልማሶች መሰረታዊ ትምህርት ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ ገመቺስ ፈቃዱ በተፋጠነ  ትምህርት  ፕሮግራም እድሜያቸው ከ9-14  ክልል ውስጥ የሚገኙ ልጆች (Over-Aged Children) ያለፋቸውን በትምህርት እድሜ ማግኘት የሚገባቸውን ትምህርት በተፋጠነ ክፍለ ጊዜ  የተሰጣቸውን የትምህርት አጠናቀው ወደ መደበኛ ትምህርት መርሐ ግብር የሚሸጋገሩበት አማራጭ  መሆኑን ጠቁመው የተፋጠነ የትምህርት መርሃ-ግብር ጥራቱን በጠበቀ መልኩ እንዲተገበር ለማስቻል ቢሮው በተለያየ ጊዜ ምልከታ እንደሚያካሂድ ጠቁመዋል::

ዳይሬክተሩ አያይዘውም የትምህርት ዕድል ሳያገኙና የማንበብ፣ የመፃፍና የማስላት ክህሎቶችን ሳይጨብጡ ትምህርት ያቋረጡ ሕፃናት ከእድሜ ጓደኞቻቸው ጋር ተመጣጣኝ ደረጃ ላይ እንዲሆኑ ለማስቻልና የአንደኛ ደረጃ ትምህርትን እንዲያገኙ አማራጭ ሥርዓት መሆኑን አንስተው አተገባበሩ በተገቢ መንገድ እየተካሄደ መሆኑን ተናግረዋል::

.

Copyright © All rights reserved.