የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ትምህርት ቢሮ ልዩ ፍላጎት ላላቸው ተማሪዎች ለመማር ማስተማር ሂደት አጋዥ የሆኑ ግብዓቶች ድጋፍ አድርጓል፡፡
ቢሮው ለአይነስውራን እና ልዩ ፍላጎት ላላቸው ተማሪዎች የብሬል ወረቀት፤ ዊልቼር፤ ክራንች እና ለአይነስውራን ተማሪዎች የሚያገለግሉ ልዩ ልዩ ግብአቶች ድጋፍ ባደረገበት ወቅት በየክፍለከተማው የተደራጁ ሪሶርስ ማእከላት ስር ለሚገኙ ትምህርት ቤቶችን የበለጠ በማጠናከር እንዲሁም ተማሪዎች የተሻለ ትምህርት እንዲያገኙና የአካል ጉዳታቸው ሳይገድባቸው ትምህርታቸውን እንዲከታተሉ ቢሮው ትኩረት እየሰራ እንደሚገኝ ተገልፃል፡፡
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ትምህርት ቢሮ ኃላፊ ዶክተር ዘላለም ሙላቱ ከታችኛው ትምህርት እርከን እስከ ከፍተኛ ደረጃ ያሉ ትምህርት ቤቶች ለተማሪዎች ምቹ የመማሪያ አካባቢ እንዲሆኑ ቢሮው በርካታ ስራዎች እያከናወነ መቆየቱን ጠቅሰው አሁንም ይህን ስራ አጠናክሮ ለመቀጠል ለአይነስውራን እንዲሁም ልዩ ፍላጎት ያላቸው ተማሪዎችን ለመደገፍ ልዩ በጀት በመመደብ እየሰራ እንደሆነ አብራርተዋል፡፡
ዶክተር ዘላለም አያይዘውም ዛሬ ተደራሽ የምናደርጋቸው ድጋፍ መስጫ ግብአቶች ለተማሪዎች ዝግጅት ለማድረግ መምህራን ደግሞ ለተማሪዎች ድጋፍ ማድረግ እንዲችሉ አቅም በመፍጠር የሚያግዝ መሆኑን ገልጸው ፤ተማሪዎች ከእድሜ እኩዮቻቸው እኩል ለትምህርት ስኬታማነት ዝግጅት እንዲያደርጉ ያስችላል ብለዋል፡፡ ቢሮ ኃላፊው አክለውም የተማሪዎች ስኬት የወላጆችን ያላሰለሰ ድጋፍ የሚጠይቅ መሆኑን በማውሳት ልጆቻችሁ መድረስ የሚፈልጉት ቦታ እንዲደርሱ ባለድርሻ አካላትን በማሳተፍ ውጤታማ የመማር ማስተማር ስርአት እንዲኖር ጠንክረን እንሰራለን ብለዋል፡፡
በግብአት ርክክቡ ወቅት የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ትምህርት ቢሮ ኃላፊ ዶክተር ዘላለም ሙላቱና የቢሮው ማኔጅመንት አባላት ፤መምህራን፤ ተማሪዎችና ወላጆች እንዲሁም የአካል ጉዳተኛ ማህበር አባላት ተገኝተዋል፡፡