የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ትምህርት ቢሮ ከኢትዮጵያ ሴንተር ፎር ዲቨሎፕመንት (ECD) ሀገር በቀል ተቋም ጋር በመተባበር ባደረገው የስራ ትብብር ውል መሰረት በአቡነ ባስልዮስ ቅድመ አንደኛ አንደኛና መካከለኛ ደረጃ ትምህርት ቤት በፔስታሎዚ ሕፃናት መርጃ ፋውንዴሽን ድጋፍ ያስገነባውን ባለ 12 ቀዳዳ የሴት ተማሪዎች መፀዳጃ ቤት ርክክብ አካሂዷል::
የኢትዮጵያ ሴንተር ፎር ዲቨሎፕመንት (ECD) በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የሚገኙ 12 ቅድመ አንደኛ አንደኛና መካከለኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ጥራቱን የጠበቀ ፣ አካታችና ፍትሐዊ ትምህርት ለማዳረስ እየሰራ የሚገኝ ድርጅት መሆኑ የተገለፀ ሲሆን ፕሮጀክቱ ከፔስታሎዚ የሕፃናት መርጃ ድርጅት (PCF) በተገኘ ገንዘብ ድጋፍ በአቡነ ባስልዮስ ትምህርት ቤት ላይ የነበረዉን የመፀዳጃ ቤት እጥረት ለመቅረፍ 3.5 ሚሊዮን የሚሆን ብር በመመደብ እንዲሁም አቡነ ባስልዮስን ጨምሮ ለ 8 ፕሮጀክት አጋር ትምህርት ቤቶች 3.2 ሚሊዮን ብር በመመደብ የላይብረሪ ፣ ላብራቶሪ ፣ አይ ሲ ቲ እና ትምህርት ማበልፀጊያ ማዕከላትና ክበባት የሚሆኑ ግብዓቶች ድጋፍ አድርጓል::
የኮልፌ ቀራንዮ ክፍለከተማ ትምህርት ፅ/ቤት ኃላፊ አቶ ገነነ ዘውዴ በመፀዳጃ ቤትና ግብዓት ርክክብ መርሐግብሩ ላይ ተገኝተው እንዳሉት ትምህርት የአንድ ተቋም ብቻ ሳይሆን የሁሉንም ማህበረሰብ ድጋፍ የሚጠይቅ መሆኑን ገልፀው ትምህርት ቤቶች ያለባቸውን ጉድለት እንዲሞሉና የትምህርት ስራን ውጤታማ ለማድረግ መንግስት በርካታ ሥራዎች እየሰራ መሆኑን ተናግረዋል ::
አቶ ገነነ አያይዘውም የትምህርት ፖሊሲ በማሻሻልና ምቹ የመማሪያ ቦታ ለመፍጠር እየተሰራ ያለውን ስራ በትምህርት ለልማት እንዲሁም ECD እና መሰል ድጋፍ የሚያደርጉ ድርጅቶች ሚና ታክሎበት ትምህርት ቤቶች ለማማር ማስተማስማር ስራ ምቹና ሳቢ እንዲሆኑ መቻላቸው በተማሪዎች ውጤት ላይ እያስመዘገብን ያለነው ውጤት ማሳያ ነው ብለዋል::
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ትምህርት ቢሮ የግንባታ ክትትልና ድጋፍ ቡድን መሪ አቶ ሙሉነህ ተክለብርሃን በበኩላቸው ትምህርት ቢሮ የትምህርት ጥራትና ተደራሽነትን አቀናጅቶ እየሰራ ያለውን ስራ ለመደገፍ ECD እያደረገ ላለው አስተዋፅኦ በቢሮው ስም ምስጋና አቅርበው :: ውጤታማ ዜጋ ለማፍራት ባለድርሻ አካላት ሀላፊነታቸውን እንዲወጡ አሳስበዋል::
ፕሮጀክቱን በገንዘብ እና በቴክኒክ የሚደግፈው የፔስታሎዚ የህፃናት መረጃ ድርጅት የኢትዮጵያ ተወካይ አቶ አበበ ደምሱም ድርጅታቸው እስካሁን የተሰሩትን ሥራዎች በገንዘብና በቴክኒክ መደገፋቸውን ገልፀው ለወደፊቱም ድጋፋቸውን አጠናክረው እንደሚቀጥሉ እና የፕሮጀክቱ ሶስተኛ ፌዝ እንደሚቀጥል በመግለፅ የተሰራው መፀዳጃ ቤትና የተሰጠው ግብዓት ለታለመለት ዓላማ እንዲውል አሳስበዋል ።
የECD ትምህርት ፕሮጀክት ኃላፊ አቶ ደመላሽ አድማሱ ፕሮጀክቱ እስከዛሬ በነበረው ቆይታ የሰራቸውንና በቀጣይ ከትምህርት ቤቶች ጋር በጋራ የሚሰራቸውን ሥራዎች እቅድ የያዘ ሰነድ ለተሳታፊዎች አቅርበዋል:: በቀጣይም በፕሮጀክቱ ርክክብ የተደረጉ ቁሳቁሶች አገልግሎት ላይ መዋላቸውንና የአጠቃቀም ሁኔታቸው ላይ ድጋፍና ክትትል እንደሚያደርግ ተናግረዋል ::
በስነሥርዓቱ ላይ የኮልፌ ቀራንዮ ክፍለከተማ ትምህርት ፅ/ቤት ኃላፊ አቶ ገነነ ዘውዴ: የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ትምህርት ቢሮ የግንባታ ክትትልና ድጋፍ ቡድን መሪ አቶ ሙሉነህ ተክለብርሃን ፣ የኮልፌ ቀራንዮ ክፍለ ከተማ ወረዳ 1 ዋና ስራ አስፈፃሚ አቶ አበባው ምህረት ፣ የECD ትምህርት ፕሮጀክት ኃላፊ አቶ ደመላሽ አድማሱ የፔስታሎጂ ፕሮጀክት አስተባባሪ አቶ አበበ ደምስ እና የትምህርት ቤቱ ተማሪዎችና መምህራን ተገኝተዋል ::
.