Announcement ትምህርት ቤቶች በአየር ንብረት ለውጥ ላይ ለሚሰሯቸው ሥራዎች ድጋፍ የሚያደርጉ ቁሳቁሶች ርክክብ ተደረገ::

ትምህርት ቤቶች በአየር ንብረት ለውጥ ላይ ለሚሰሯቸው ሥራዎች ድጋፍ የሚያደርጉ ቁሳቁሶች ርክክብ ተደረገ::

26th July, 2025

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ትምህርት ቢሮ ከሴንተር ፎር ዲቨሎፕመንት (ECD) ጋር ባደረገው የስራ ትብብር ስምምነት ውል መሰረት  በMobil Toolkit For Climate Resilience (MTCR )ፕሮጀክት አማካኝነት በለሚኩራ ፣ ለየካ እና ኮልፌ ቀራንዮ ክፍለ ከተሞች ለሚገኙ 6 ትምህርት ቤቶች በአየር ንብረት ለውጥ ዙሪያ ለሚሰሩ ሥራዎች ድጋፍ የሚሆኑ ቁሳቁሶች ርክክብ ተደርጓል::

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ትምህርት ቢሮ የፕሮጀክት ዝግጅት ክትትል ግምገማ ከፍተኛ ባለሙያ አቶ ታረቀኝ ወ /ሀና በፕሮጀክቱ ድጋፍ ለተደረጉ ቁሳቁሶች በቢሮው ስም ምስጋና አቅርበው ትምህርት ቤቶቹ ቁሳቁሶቹን ለታለመላቸው አላማ እንዲያውሉ አሳስበዋል::

የኢትዮጵያ ሴንተር ፎር ዲቨሎፕመንት (ECD) ዋና ዳይሬክተር ወ/ሮ ሐረገወይን አሸናፊ በርክክቡ ላይ ተገኝተው እንዳሉት ትምህርት ቤቶቹ በአየር ንብረት ለውጥ ዙሪያ እንዲሁም የጓሮ አትክልት ልማት ሥራዎችን ለማሻሻል እያደረጉ ላለው ሥራ አጋዥ የሚሆኑ ቁሳቁሶች በ(MTCR )ፕሮጀክት አማካኝነት በፔስታሎዚ የሕፃናት መርጃ ድርጅት (PCF) በተገኘ ገንዘብ ድጋፍ የቁሳቁስ ርክክብ መደረጉን ገልፀው በቀጣይም በአየር ለውጥ ዙሪያ በትምህርት ቤቶች በመገኘት ለተማሪዎች ስልጠናና ግንዛቤ ማስጨበጫ ሥራዎች ለመስራት ሰፊ እቅድ መያዙን ገልፀዋል:: አያይዘውም ድጋፉ ትምህርት ቤቶች የአየር ንብረት ለውጥና የከተማ ግብርና ሥራዎችን አጠናክረው እንዲሰሩ ያበረታታል ብለዋል ::

የMobil Toolkit for Climate Resilience (MTCR) ፕሮጀክት አስተባባሪ አቶ ደመላሽ አድማሱ ፕሮጀክቱ በቀጣይ ከትምህርት ቤቶች ጋር በጋራ የሚሰራቸውን ሥራዎች እቅድ የያዘ ሰነድ አቅርበዋል:: በቀጣይም በፕሮጀክቱ ርክክብ የተደረጉ ቁሳቁሶች አገልግሎት ላይ መዋላቸውን በድጋፍና ክትትል ውጤታማነታቸውን እንደሚመዝን ተናግረዋል ::

በርክክቡ ከስድስቱ ትምህርት ቤቶች ውስጥ የውሃ እጥረት ላለባቸው ጎዴ ፣ የማነ ብርሀን እና አጃንባ ትምህርት ቤቶች 10ሺ ሊትር የውሃ ማጠራቀሚያ ታንከር ጨምሮ አጠቃላይ 3.8 ሚሊየን ብር ወጪ የሆነበት የጓሮ አትክልት ዘሮች ፣ የውሃ ማጠጫና መኮትኮቻ ፣ ግንዛቤ ማስጨበጫ ኤሌክትሮኒክስ ዕቃዎች እና የአየር ንብረት ለመጠበቅ የሚረዱ ቁሳቁሶች ድጋፍ አድርገዋል ::

ርክክቡ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ትምህርት ቢሮ ፕሮጀክት ዝ/ክ/ግ ከፍተኛ ባለሙያ አአቶ ታረቀኝ ወልደ ሀና ጨምሮ የኢትዮጵያ ሴንተር ፎር ዲቨሎፕመንት (ECD) ዋና ዳይሬክተር ወ/ሮ ሐረገወይን አሸናፊ የ6ቱ ትምህርት ቤቶች ዳይሬክተሮች ፣ የወ.ተ.መ አባላት ተገኝተዋል::

.

Copyright © All rights reserved.