የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ትምህርት ቢሮ "የትምህርት ግብዓት ለትምህርት ቤቶች ውጤታማ ትራንስፎርሜሽን!" በሚል መሪ ቃል 137 የቅድመ አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶችን ትራንስፎርም ለማድረግ የሚያስችሉ የተለያዩ ግብአቶችን በመግዛት ለተቋማቱ አሰራጨ።
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ትምህርት ቢሮ ምክትል ቢሮ ኃላፊና የዘርፉ አስተባባሪ አቶ ጥላዬ ዘውዴ በመርሀግብሩ ባስተላለፉት መልዕክት ትምህርት ቢሮ በከተማ አስተዳደሩ የሚገኙ የቅድመ አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶችን ትራንስፎርም ለማድረግ ባከናወናቸው የተለያዩ ተግባራት እስካሁን 115 ያህሉ ትራንስፎርም ማድረጋቸውን በተቋማቱ በተካሄደ ምዘና መረጋገጡን አስታውሰው ትምህርት ቤቶቹ ግብአት ማሟላታቸው በጫወታ የማስተማር ስነ ዘዴን ተግባራዊ አድርገው ሞዴል እንዲሆኑ የሚያስችል መሆኑን አስገንዝበዋል።
ምክትል ቢሮ ኃላፊው አያይዘውም የቅድመ አንደኛ ደረጃ ትምህርት ህጻናቱ ለቀጣይ የትምህርት ዘመናቸው መሰረት የሚይዙበት እንደመሆኑ በዛሬው እለት ግብአት የተሰራጨላቸው ተቋማት ግብአቶቹን ለሚፈለገው አላማ በማዋል ተማሪዎችን ተጠቃሚ እንዲያደርጉ ጥሪ አቅርበዋል።
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ትምህርት ቢሮ የዘርፈ ብዙና ቀዳማይ ልጅነት ትግበራ ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ወይዘሮ በላይነሽ የሻው በበኩላቸው ቢሮው የቅድመ አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ትራንስፎርም እንዲያደርጉ ከግብአት ስርጭት ባሻገር ለመምህራንና ርዕሳነ መምህራን ተደጋጋሚ የአቅም ግንባታ ስልጠና ሲሰጥ መቆየቱን ጠቁመው ቢሮው በቀጣይ በዛሬው እለት የተሰራጩ ግብአቶች በአግባቡ አገልግሎት ላይ መዋላቸውን በተቋማቱ በመገኘት በድጋፍና ክትትል የሚያረጋግጥ መሆኑን አስታውቀዋል።