የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ትምህርት ቢሮ የአገልግሎት አሰጣጥ መማክርት ጉባኤ ተግባር እና ኃላፊነት ዙሪያ ከጉባኤው አባላት ጋር ውይይት አካሂዷል።
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ትምህርት ቢሮ ኃላፊ ዶክተር ዘላለም ሙላቱ በውይይቱ መክፈቻ ባስተላለፉት መልዕክት ቢሮው ከተለያዩ ባለድርሻ አካላት ጋር በቅንጅት በመስራቱ በመማር ማስተማር ሂደቱ ተጨባጭ ውጤት መመዝገቡን ገልጸው የአገልግሎት አሰጣጥ መማክርት ጉባኤው ቢሮው የሚሰጠው አገልግሎት ተሻሽሎ በትምህርት ተቋማት ውጤታማ የመማር ማስተማር ሂደት እንዲኖር በጉባኤው የማቋቋሚያ ማኑዋል በተቀመጠው መሰረት ኃላፊነት እና ተግባራቸውን በአግባቡ እንዲወጡ ጥሪ አቅርበዋል።
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ትምህርት ቢሮ የቢሮ ኃላፊ አማካሪ ወይዘሮ አበበች ነጋሽ በበኩላቸው ቢሮው የሚያከናውናቸው ተግባራት የተገልጋዩን እርካታ እንዲያሻሽሉ እና ከህብረተሰቡ የሚነሱ ጥያቄዎች ተገቢውን ምላሽ እንዲያገኙ የአገልግሎት አሰጣጥ መማክርት ጉባኤው መቋቋሙን ጠቁመው ቢሮው በቀጣይ ከጉባኤው አባላት ጋር የቅርብ ግንኙነት እየፈጠረ የተከናወኑ ተግባራትን እንደሚገመግም አስገንዝበዋል።
የአገልግሎት አሰጣጥ መማክርት ጉባኤ(የተገልጋይ ካውንስል) ከተገልጋይ ግለሰቦች የሚወከሉ አባላትን ጨምሮ ከሲቪክ ማህበራት፣ ከባለድርሻ ተቋማት እንዲሁም ከትምህርት ቢሮ ጉዳዩ የሚመለከታቸው የስራ ኃላፊዎችን አካቶ መቋቋሙን የሪፎርም አገልግሎት አሰጣጥ ክትትልና ምዘና ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ ፈንታሁን እያዩ አመላክተዋል።
.