(ሀምሌ 27/2018 ዓ.ም) የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ትምህርት ቢሮ የልዩ ፍላጎትና ጎልማሶች መሰረታዊ ትምህርት ዳይሬክቶሬት ለተፋጠነ ትምህርት አገልግሎት የተዘጋጀ የተማሪዎች መማሪያ መጽሐፍ በመምህራን እና በትምህርት ባለሙያዎች በማስገምገም ላይ መሆኑን አስታወቀ።
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ትምህርት ቢሮ የልዩ ፍላጎትና ጎልማሶች መሰረታዊ ትምህርት ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ ገመቺስ ፍቃዱ የመማሪያ መጽሐፉ በአዲሱን ስርአተ ትምህርት መነሻ መዘጋጀቱን ጠቁመው ትምህርቱ የተጨመቀ ስርአተ ትምህርትን መሰረት አድርጎ እድሜያቸው ከ9 እስከ 14 ለሆኑ ተማሪዎች እየተሰጠ መሆኑን አስረድተዋል።
ዳይሬክተሩ አያይዘውም በግምገማው ከተሳተፉ መምህራንና የትምህርት አመራሮች የሚሰጡ የማስተካከያ ሀሳቦችን በማካተት መጽሐፉ ታትሞ በ2019 የትምህርት አመት ለአገልግሎት እንዲበቃ በትኩረት እየተሰራ መሆኑን ገልጸው በከተማ አስተዳደሩ ከ3,200 በላይ ተማሪዎች በተፋጠነ የትምህርት አገልግሎት ተጠቃሚ መሆናቸውን አመላክተዋል።
የተፋጠነ ትምህርት እድሜያቸው ከ9 እስከ 14 አመት ሆኖ በተለያዩ ምክንያቶች የመማር እድል ላላገኙ የህብረተሰብ ክፍሎች ለአንድ አመት የሚሰጥ ሲሆን ተማሪዎቹ ትምህርቱን ተከታትለው ሲያጠናቅቁ 4ኛ ክፍል ገብተው መደበኛውን ትምህርት የሚማሩበት አማራጭ መዘጋጀቱን አቶ ገመቺስ አስገንዝበዋል።
.