የመምህራኑ ዝውውር እና ሽግሽግ የሰው ሀይልን አመጣጥኖ በመጠቀም የመማር ማስተማር ስራውን ውጤታማ ለማድረግ ታስቦ የክፍለ ከተማ የመምህራን እና የትምህርት አመራር ልማት ቡድን መሪዎችና ተወካይ ባለሙያዎች እንዲሁም የአዲስ አበባ መምህራን ማህበር አመራሮች እና ጉዳዩ የሚመለከታቸው የቢሮ ባለሙያዎች በተገኙበት በማዕከል ደረጃ እየተካሄ እንደሚገኝ ከቢሮው የመምህራን እና የትምህርት አመራር ልማት ዳይሬክቶሬት ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ትምህርት ቢሮ የመምህራን እና የትምህርት አመራር ልማት ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ ተስፋዬ አበራ የመምህራኑ ዝውውርና ሽግሽግ ቀደም ሲል በማመልከቻ ለጠየቁ መምህራን በግልጽ የተቀመጠ የዝውውር መመሪያን መሰረት አድርጎ እየተካሄደ መሆኑን ጠቁመው ዝውውሩ የአዲስ አበባ መምህራን ማህበር ተወካዮች በተገኙበት በጥንቃቄ እና በጥብቅ ዲሲፒሊን በመካሄድ ላይ መሆኑን አስታውቀዋል።
ዳይሬክተሩ አያይዘውም መምህራኑ ባላቸው የስራ ልምድና የትምህርት ዝግጅት ተወዳድረው አሸናፊ የሚሆኑት በየክፍለ ከተማው በሚገኙ የቅድመ አንደኛ፣አንደኛ እና ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች እንደሚመደቡ ጠቁመው ልዩ ፍላጎት ያላቸው መምህራን በልዩ ሁኔታ ቅድሚያ የሚሰጣቸው መሆኑንም አመላክተዋል።
ዝውውሩ ለተከታታይ አምስት ቀናት ተሰርቶ ሲጠናቀቅ ለክፍለ ከተሞች የሚላክ መሆኑን አቶ ተስፋዬ ጠቅሰው ክፍለ ከተማ ወደ ክፍለ ከተማ የሚደረግ የመምህራን ዝውውር እንዳስፈላጊነቱ በአመት ሁለት ጊዜ የሚካሄድ መሆኑን አስገንዝበዋል።