(ሰኔ 23/2018 ዓ.ም) ፈተናው በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በ131 ጣቢያዎች በበይነ መረብ እየተሰጠ የሚገኝ ሲሆን የኢፌድሪ ትምህርት ሚኒስቴር ፕሮፌሰር ብርሀኑ ነጋ ከሚኒስቴር ዴኤታ ወይዘሮ አየለች እሸቴ እንዲሁም ከአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ትምህርት ቢሮ ኃላፊ ዶክተር ዘላለም ሙላቱ እና ከምክትል ቢሮ ኃላፊ አቶ ሳምሶን መለሰ ጋር በመሆን ፈተናው ከሚሰጥባቸው ጣቢያዎች መካከል በአብረሖት ላይብረሪ ተገኝተው የፈተናውን አጀማመር በመመልከት ተማሪዎችን አበረታተዋል።
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ትምህርት ቢሮ ኃላፊ ዶክተር ዘላለም ሙላቱ ሀገር አቀፉ የ12ኛ ክፍል መልቀቂያ ፈተና በአዲስ አበባ ከተማ በሚገኙ 131 የፈተና ጣቢያዎች በበይነ መረብ ያለምንም እንከን መጀመሩን ጠቁመው ፈተናው ስኬታማ ሆኖ እንዲጠናቀቅ በሁሉም የፈተና ጣቢያዎች በቂ ኮምፒውተሮችን ጨምሮ የኢንተርኔት አገልግሎት እንዲኖር ቢሮው ከሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ጋር በቅንጅት ሲሰራ መቆየቱን አመላክተዋል።
ኃላፊው አያይዘውም በከተማ አስተዳደሩ ፈተናው ለ58,309 ተማሪዎች በአራት ዙር የሚሰጥ መሆኑን ጠቅሰው ከ2ሺ በላይ የፈተና አስፈጻሚዎች በየፈተና ጣቢያው ተመድበው ሂደቱን በመከታተል ላይ መሆናቸውን በመግለጽ ለተፈታኝ ተማሪዎች የመልካም ምኞት መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል።


.