የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ትምህርት ቢሮ በ2018 ዓ.ም የበጀት አመት በቁልፍና አበይት ተግባራት የተከናወኑ ዋና ዋና ተግባራትን ርዕሳነ መምህራንን ጨምሮ በየደረጃው የሚገኙ የትምህርት አመራሮች በተገኙበት በአድዋ ድል መታሰቢያ ሙዚየም በሚገኘው ፓን- አፍሪካ አዳራሽ ገምግሟል።የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ትምህርት ቢሮ ኃላፊ ክቡር ዶክተር ዘላለም ሙላቱ በመርሀግብሩ ባስተላለፉት መልዕክት በ2018 ዓ.ም የትምህርት አመት ቢሮው ባለድርሻ አካላትን በማስተባበር ባከናወናቸው ተግባራት የትምህርት ልማት ስራው ውጤታማ እንዲሆን ማስቻሉን አመላክተዋል።ኃላፊው አያይዘውም በቀጣይ የሚሰጡ ከተማ አቀፍ እና ሀገር አቀፍ ፈተናዎች ስኬታማ ሆነው እንዲጠናቀቁ በየደረጃው የሚገኙ የትምህርት አመራሮች ኃላፊነታቸውን በአግባቡ መወጣት እንደሚገባቸው በመጠቆም በተለይም የ12ኛ ክፍል መልቀቂያ ብሔራዊ ፈተናን በሚያስፈትኑ ጣቢያዎች የአይ ሲቲ መሰረተ ልማትን ጨምሮ በቂ ግብአቶችን በማሟላት ለፈተናው ዥግጁ እንዲሆኑ በቂ ክትትልና ድጋፍ ማድረግ የሚገባ መሆኑን አስገንዝበዋል።የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ትምህርት ቢሮ ምክትል ቢሮ ኃላፊ አቶ ተስፋዬ አበራ በበኩላቸው የዛሬው መርሀግብር በከተማ አስተዳደሩ በ2018ዓ.ም የትምህርት አመት የተከናወኑ ተግባራትን በመገምገም በቀጣይ የማጠቃለያ ምዕራፍ ቀሪ ተግባራትን በማከናወን የተማሪዎች ውጤትና ስነምግባር እንዲሻሻል የትምህርት አመራሩ ኃላፊነቱን በአግባቡ እንዲወጣ የሚያስችል መሆኑን አመላክተዋል።ቢሮው የበጀት አመቱን እቅድ ከሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ጋር በጋራ በማፅደቅ ወደ ተግባር ከመግባት ባሻገር በየሩብ አመቱ አፈጻጸሙን በመገምገም ቀጣይ አቅጣጫ ሲያስቀምጥ መቆየቱን የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ትምህርት ቢሮ የቢሮ ኃላፊ አማካሪ ወይዘሮ አበበች ነጋሽ ገልጸው በበጀት አመቱ በቁልፍና አበይት ተግባራት የተመዘገበው አፈጻጸም በጣም ከፍተኛ ደረጃ ላይ እንደሚገኝ በግምገማ መረጋገጡን አስታውቀዋል።በመርሀግብሩ ክልል አቀፍን እና ሀገር አቀፉን ፈተና ስኬታማ ለማድረግ እየተከናወኑ የሚገኙ የቅድመ ዝግጅት ተግባራት በምክትል ቢሮ ኃላፊው አቶ ተስፋዬ አበራ እንዲሁም የበጀት አመቱ የቁልፍና አበይት ተግባራት ሪፖርት በእቅድና በጀት ዳይሬክተር አቶ ጌታሁን ለማ ቀርቦ በተሳታፊዎች ውይይት ከመካሄዱ ባሻገር በቀጣይ የርብርብ ማዕከል ሆነው የሚከናወኑ ተግባራትን መሰረት በማድረግ አቅጣጫ ተቀምጧል።
.