በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በ2018 የትምህርት ዘመን 97.48% የሚሆኑ የ6ኛ ክፍል ተማሪዎች 50% እና በላይ በማስመዝገብ ወደ ቀጣዩ የክፍል ደረጃ ተዘዋወሩ፡፡
(ሰኔ 29/2018 ዓ.ም) በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር 2018 ዓ.ም የትምህርት ዘመን 97.48 % የሚሆኑ የ6ኛ ክፍል ተማሪዎች 50% እና በላይ በማስመዝገብ ወደ ቀጣዩ የክፍል ደረጃ መሸጋገራቸውን የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ትምህርት ቢሮ ኃላፊ ክቡር ዶክተር ዘላለም ሙላቱ አስታወቁ።
ኃላፊው የ2018 የትምህርት ዓመት የ6ኛ ክፍል መልቀቂያ ፈተና ውጤት ይፋ መሆኑን በማስመልከት ለተለያዩ የሚዲያ ተቋማት ጋዜጣዊ መግለጫ ሰተዋል።
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ትምህርት ቢሮ ኃላፊ ክቡር ዶክተር ዘላለም ሙላቱ በጋዜጣዊ መግለጫቸው በከተማ አስተዳደሩ የ2018 ዓ.ም የ6ኛ ክፍል መልቀቂያ ፈተና ከወሰዱ 84,257 ተማሪዎች መካከል 82,137 የሚሆኑ ተማሪዎች 50 በመቶ እና በላይ በማስመዝገብ ወደ ቀጣዩ የትምህርት እርከን መሸጋገራቸውን አስታውቀዋል።
ኃላፊው አያይዘውም ዘንድሮ 97.48% የሚሆኑ ተማሪዎች 50 እና በላይ በማምጣት ወደ ዘጠነኛ ክፍል ያልፉበት ውጤት በ2017 ዓ.ም ከነበረው 95% አንጻር እድገት ማሳየቱን ገልጸው ውጤቱ እንዲመዘገብ ኃላፊነታቸውን በአግባቡ ለተወጡ መምህራን ፣ የትምህርት አመራሮችና ባለሙያዎች እንዲሁም ለወላጆችና ለሌሎች ባለድርሻ አካላት ምስጋና አቅርበዋል።