(ሰኔ 11/2018 ዓ.ም) በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ሰኔ 11 እና ሰኔ 12/2018 ዓ.ም የሚሰጠው የ2018 ዓ.ም የ8ኛ ክፍል መልቀቂያ ፈተና በ201 የፈተና ጣቢያዎች በዛሬው እለት ተጀምሯል።
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ትምህርት ቢሮ ኃላፊ ክቡር ዶክተር ዘላለም ሙላቱ ፈተናው ሰላማዊ ሆኖ ያለምንም እንከን እንዲጠናቀቅ ቀደም ብሎ ኮማንድ ፖስት ከማደራጀት ጀምሮ ልምድ ያላቸውን የፈተና አስፈጻሚዎች በመመልመል በየፈተና ጣቢያው መመደቡን የፈተናውን አጀማመር ለመመልከት ከአዲስ ከተማ ክፍለ ከተማ ዋና ስራ አስፈጻሚ አቶ ታረቀኝ ወርቅነህ ፣ ከምክትል ቢሮ ኃላፊ አቶ ሳምሶን መለሰ እንዲሁም ከክፍለ ከተማው ትምህርት ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ብሩክ ተክለማርያም ጋር በመሆን በዳግማዊ ብርሀን አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት በተገኙበት ወቅት አስታውቀዋል።
በከተማ አስተዳደሩ 86,783 የ8ኛ ክፍል ተማሪዎች ፈተናውን ለመውሰድ ተመዝግበው ዝግጅት ሲያደርጉ መቆየታቸውን ጠቁመው በሁሉም የፈተና ጣቢያዎች የፈተናውን ሂደት የሚከታተሉ አመራሮችን ጨምሮ የጸጥታ አካላትና የፈተና አስፈጻሚዎች መመደባቸውን አመላክተዋል።
ተማሪዎች ውጤታማ እንዲሆኑ በየትምህርት ቤቱ የማጠናከሪያ ትምህርት ከመሰጠቱ ባሻገር ደረጃውን የጠበቀ የሞዴል ፈተና እንዲወስዱ መደረጉን ገልጸው ፈተናው ከኩረጃ ነጻ እንዲሆን ለተማሪዎችና የፈተና አስፈጻሚዎች ኦረንቴሽን መሰጠቱን አመላክተዋል።
በአዲስ ከተማ ክፍለ ከተማ በ18 የፈተና ጣቢያዎች 7,893 ተማሪዎች ፈተናውን ለመውሰድ መመዝገባቸውን የክፍለ ከተማው ዋና ስራ አስፈጻሚ አቶ ታረቀኝ ወርቅነህ ገልጸው ፈተናው በሁሉም ጣቢያዎች ሰላማዊ ሆኖ እንዲጠናቀቅ ክፍለ ከተማው በትኩረት በመስራት ላይ መሆኑን አስታውቀዋል።

.