በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከሰኔ 8 እስከ ሰኔ 10/2018 ዓ.ም የሚሰጠው የ2018 ዓ.ም የ6ኛ ክፍል መልቀቂያ ፈተና በ በ199 የፈተና ጣቢያዎች በዛሬው እለት ተጀምሯል።
ፈተናው ሰላማዊ ሆኖ እንዲጠናቀቅ በየደረጃው የኮማንድ ፖስት አደረጃጀት የማዋቀር እና ልምድ ያላቸውን የፈተና አስፈጻሚዎች በመመልመል በየፈተና ጣቢያው ከመመደብ ጀምሮ የተለያዩ የቅድመ ዝግጅት ተግባራት መከናወናቸውን የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ትምህርት ቢሮ ኃላፊ ክብር ዶክተር ዘላለም ሙላቱ ገልጸዋል፡፡ቢሮ ሀላፊው ከአራዳ ክፍለ ከተማ ዋና ስራ አስፈጻሚ ከአቶ ወንድሙ ኡመር ፣ ከምክትል ቢሮ ኃላፊ ከአቶ ሳምሶን መለሰ እና ከአራዳ ክፍለ ከተማ ትምህርት ጽህፈት ቤት ኃላፊ ከአቶ ዱጋሳ ፍቃዱ ጋር በመሆን በዳግማዊ ሚኒሊክ አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት በመገኘት ፈተናዉን አስጀምረዋል፡፡
ቢሮ ሀላፊው በከተማ አስተዳደሩ 85,017 የ6ኛ ክፍል ተማሪዎች ፈተናውን ለመውሰድ ተመዝግበው ዝግጅት ሲያደርጉ መቆየታቸውን ጠቁመው በሁሉም የፈተና ጣቢያዎች የፈተናውን ሂደት የሚከታተሉ አመራሮችን ጨምሮ የጸጥታ አካላትና የፈተና አስፈጻሚዎች መመደባቸውን አመላክተዋል።በከተማ አስተዳደሩ የተማሪዎች የምገባ አገልግሎት ተግባራዊ መሆኑ እንዲሁም ዩኒፎርምን ጨምሮ የተለያዩ የመማሪያ ቁሳቁስ ድጋፍ መደረጉ በየአመቱ የተማሪዎች ውጤት እንዲሻሻል ከፍተኛ አስተዋጽኦ ማድረጉን ኃላፊው አስታውሰው ዘንድሮ ከተደረገው የቅድመ ዝግጅት ስራ አንጻር በ6ኛ ክፍል የተሻለ ውጤት እንደሚጠበቅ አስገንዝበዋል።በአራዳ ክፍለ ከተማ በ11 የፈተና ጣቢያዎች 3,739 ተማሪዎች ፈተናውን ለመውሰድ መመዝገባቸውን የክፍለ ከተማው ትምህርት ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ዱጋሳ ፍቃዱ ገልጸው ፈተናው በሁሉም ጣቢያዎች ሰላማዊ ሆኖ እንዲጠናቀቅ ጽህፈት ቤቱ ከባለድርሻ አካላት ጋር በቅንጅት በመስራት ላይ መሆኑን አስታውቀዋል።