About የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ካቢኔ በቅርቡ ባጸደቀው የግል ትምህርት አገልግሎት ክፍያ አሰራር ስርአት ደንብ ቁጥር 194/2017 ዙሪያ መንግስታዊ ካልሆኑ የትምህርት ተቋማት ጋር ውይይት ተካሄደ።

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ካቢኔ በቅርቡ ባጸደቀው የግል ትምህርት አገልግሎት ክፍያ አሰራር ስርአት ደንብ ቁጥር 194/2017 ዙሪያ መንግስታዊ ካልሆኑ የትምህርት ተቋማት ጋር ውይይት ተካሄደ።

14th June, 2025

(ሰኔ 5/2017 ዓ.ም) በመርሀ ግብሩ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ትምህርት ቢሮ ኃላፊ ዶክተር ዘላለም ሙላቱ ፣ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የትምህርትና ስልጠና ቁጥጥር ባለስልጣን ዋና ስራ አስኪያጅ  አቶ ኢዘዲን ሙስባህን ፣ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የትምህርትና ስልጠና ቁጥጥር ባለስልጣን ምክትል ስራ አስኪያጅ  ወ/ሮ ታገይቱ አባቡ ፣ የግል ትምህርት ቤቶች አሰሪዎች ማህበር ፕሬዝደንት አቶ አበራ ጣሰውን ጨምሮ በየደረጃው የሚገኙ የትምህርትና ስልጠና ቁጥጥር ባለስልጣን አመራሮች ፣ እንዲሁም የግል ትምህርት ቤት ባለቤቶች እና የተማሪ ወላጅ ኮሚቴ ተወካዮች የተሳተፉ ሲሆን የባለስልጣኑ የዕውቅና ፍቃድ እድሳት ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ ያሬድ ካሳ ረቂቅ ደንቡን አቅርበው ውይይት ተካሂዷል።

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ትምህርት ቢሮ ኃላፊ ዶክተር ዘላለም ሙላቱ በመርሀግብሩ መክፈቻ ባስተላለፉት መልዕክት መንግስት የትምህርት ተደራሽነትን ለማረጋገጥ እያከናወነ ከሚገኘው ተግባር ጎን ለጎን የግል ትምህርት ተቋማትም የከተማው ነዋሪ የትምህርት አገልግሎቱ ተጠቃሚ እንዲሆን እያበረከቱ ያለው አስተዋጽኦ ከፍተኛ መሆኑን ጠቁመው ደንቡ በግል ትምህርት ተቋማትና በተማሪ ወላጆች መካከል ያለውን ግንኙነት በማጠናከር የመማር ማስተማር ስራውን ውጤታማ ለማድረግ መዘጋጀቱን አስታውቀዋል።

ዶክተር ዘላለም አያይዘውም የግል ትምህርት አገልግሎት ክፍያ አሰራር ስርአት ረቂቅ ደንቡ በዚህ አመት በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ጸድቆ ተግባራዊ የተደረገውን የትምህርት ህግ መነሻ አድርጎ በከተማ አስተዳደሩ ካቢኔ መጽደቁን ገልጸው ረቂቅ ደንቡ ግልጽ የሆነ እና ወቅቱን ታሳቢ ያደረገ የክፍያ ስርአት ለማስፈን የሚያስችል በመሆኑ የግል ትምህርት ተቋማት ደንቡ  ተግባራዊ እንዲሆን የሚጠበቅባቸውን ኃላፊነት በአግባቡ መወጣት እንደሚገባቸው አስገንዝበዋል።

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የትምህርትና ስልጠና ቁጥጥር ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር አቶ ኢዘዲን ሙስባህ በበኩላቸው ረቂቅ ደንቡ የዜጎችን የመማር መብት በማረጋገጥ የወላጆችን የመክፈል አቅም እና የትምህርት ተቋማቱን የግብአት አቅርቦት ታሳቢ አድርጎ ተግባራዊ የሚደረግ መሆኑን ጠቁመው ደንቡ በዋናነት የትምህርት ተቋማቱን የኢንስፔክሽን ደረጃ ከግምት ያስገባ መሆኑን በመግለጽ የዛሬው ውይይት ከረቂቅ ደንቡ ጋር በተገናኘ ግልጸኝነት በመፍጠር ወደ ተግባር ለመግባት የሚያስችል መሆኑን አመላክተዋል።

የውይይቱ ተሳታፊ የግል ትምህርት ቤት ባለቤቶችና ተወካዮች በቀረበው ረቂቅ ደንብ ዙሪያ የተለያዩ ጥያቄዎችን እና አስተያየቶችን አቅርበው በሁለቱ ተቋማት አመራሮች ምላሽ ተሰቷል።


.

Copyright © All rights reserved.