የ12ኛ ክፍል ሀገር አቀፍ ኦንላይን ፈተና ቅድመ ዝግጅትን አስመልክቶ ምልከታ ተካሄደ::
(ግንቦት 15/2017 ዓ.ም) በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በሚገኙ የ12ኛ ክፍል ኦንላይን ፈተና መስጫ ጣቢያዎች ላይ ያለውን የቅድመ ዝግጅት ስራዎች አስመልክቶ ጉብኝት ተካሄደ፡፡
በጉብኝቱ ላይ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ትምህርት ቢሮ ምክትል ቢሮ ኃላፊ አቶ ዲናኦል ጫላ እና የቢሮ አማካሪ አቶ ጥላሁን ፈቃዱ ሀገር አቀፍ የ12ኛ ክፍል መልቀቂያ ፈተና ለመስጠት እየተደረገ ያለውን ቅድመ ዝግጅትና የተማሪዎችን ልምምድ በቂርቆስ ክፍለ ከተማ በሚገኘው አሳይ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት እና በጉለሌ ክፍለ ከተማ የሚገኘው እቴጌ መነን የልጃገረዶች አዳሪ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች በመገኘት ምልከታ አካሂደዋል፡፡
በምልከታው ተማሪዎች የኦንላይን ፈተና ልምምድ በማካሄድ ላይ መሆናቸዉ የተገለጸ ሲሆን ፤ በቅድመ ዝግጅቱ የተማሪዎች ኦንላይን ፈተና ልምምድ ፤ የመፈተኛ ክፍሎች ፤ የኮምፒውተርና ኢንተርኔት እንዲሁም ጀነሬተሮች ዝግጁነት ላይ የፈተና መስጫ ጣቢያዎቹ ያላቸው ዝግጁነትና የማስፈተን አቅም ላይ ጉብኝት ተደርጓል፡፡
በቀጣይም የመፈተኛ ጣቢያዎች ፈተናውን ለመስጠት ያላቸውን ዝግጁነት ላይ ክትትልና ድጋፍ በማድረግ ለፈተናው ውጤታማነት ቢሮው በትኩረት እየሰራ እንደሆነ የቢሮው ምክትል ቢሮ ኃላፊ አቶ ዲናኦል ጫላ ተናግረዋል፡፡